"እግዚአብሔር ማን እንደሆነ ለማወቅ ክርስቶስን ተመልከቱ። ፍቅር ምን እንደሆነ ለመረዳት ክርስቶስን ተመልከቱ። ትክክለኛ ሰው ምን እንደሆነ ለማወቅ ክርስቶስን ተመልከቱ።"
ኤን ቲ ራይት (N.T.Wright)፤ እንግሊዛዊ የነገረ መለኮት ሊቅ።
የዮሐንስ ወንጌል ፀሐፊ ኢየሱስ ይወደው የነበረው ደቀመዝሙር ዮሐንስ የዘብዴዎስ ልጅ ነው።ወንጌሉን የፃፈው ከ70-90 ባሉት አመታት ብዙ በኖረባት ከተማ በኤፌሶን ነው ተብሎ ይታመናል። ከዚህ ወንጌል በተጨማሪ ሶስቱን የዮሐንስ መልዕክቶችንና በመጨረሻም የራዕይን መፅሐፍ አበርክቶልን አልፏል። ዮሐንስ አብረውት በጌታ ከተጠሩት ሐዋርያት መካከል በሮማ ገዥ አካሉ በፈላ ዘይት ተጠብሶ የጠባሳውን ምልክት በሰውነቱ ይዞና በተዐምር ከሞት ተርፎ በፍጥሞ ደሴት በግዞት በመኖር ተፈጥሯዊ ሞትን የሞተ ብቸኛው ሐዋርያ ነው። ዮሐንስ ከሌሎቹ ወንጌላት በተለየ አፅንኦት፣በማያሻማና ገላጭ በሆነ መልኩ ለሰው ልጆች የእግዘብሔር ቃል የሆነው ወልድ ስጋ ለብሶ የተገለጠበትን ታላቁን አላማ ያስረገጠው “ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ እንድታምኑና፥ አምናችሁም በስሙ ሕይወት ይሆንላችሁ ዘንድ ይህ ተፅፏል” ሲል ባሰፈረው ሐይለ ቃሉ ነው።
የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ አንድ የክርስትና መሠረት ከሆኑት የመፅሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ውስጥ ከዋንኞቹ አንዱ ነው። በዚህ ምዕራፍ ጅማሬ ላይ ለብዙዎቻችን ተወዳጅ የሆነውና ጌታ ክርስቶስን ጉልሕ አድርጎ ያሳየንንን የመፅሀፍ ቅዱስ ጥቅስ እናገኛለን። ዮሐንስ ከጅማሬ በፊት የነበረውን መጀመርም በእርሱ የሆነውን የእግዚአብሔርን ልጅ፣የሥላሴን አካል፣ አብን የገለጠውን፣ በፍጥረት ጅማሬ ላይ ከእግዚአብሔርና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ሆኖ ይሕንን አለም ካለመኖር ወደመኖር አምጥቶ ያበጀውን ጌታን "በመጀመሪያ ቃል ነበር ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበር ያም ቃል እግዚአብሔር ነበር" ብሎ ለፍጥረታት ሁሉ ያበስረዋል። ዮሐንስ በዚሕ ወንጌሉ 98 ግዜ ያክል "ቃል" እያለ መጠቀሙ ጌታ ኢየሱስን ለሰው ልጆች ሁሉ ለማስተዋወቅ ምን ያሕል እንደተጋና እንደፈለገ ያስገነዝበናል።
የዮሐንስ ወንጌል የእግዚአብሔር አምላክ ዘልዓለማዊ ቃልና ፈጣሪ እርሱ ክርስቶስ እንደሆነ "ሁሉ በርሱ ሆነ ከሆነውም አንዳችም ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም" ብሎ በማለት እግዚአብሔር አብ ሁሉን በወልድ በኩል መፍጠሩን ያስረዳናል። የዕብራውያን
ፀሐፊም ይሕንን የዮሐንስን ቃል ሲያፀና "አለማትን በፈጠረበት በልጁ" ይለናል። የምሳሌም መፅሐፍ ክርስቶስን በጥበብ ቃል ወክሎ "ሰማዮችን በዘረጋ ግዜ አብሬ ነበርሁ.የምድርን መሠረት በመሠረተ ግዜ ያን ግዜ እኔ በእርሱ ዘንድ ዋና ሰራተኛ ነበርሁ፥
ዕለት ዕለት ደስ አሰኘው ነበርሁ፥ በፊቱ ሁልግዜ ደስ ይለኝ ነበርሁ" ብሎ ሲል ንጉሥ ዳዊትም በመዝሙሩ "እርሱ ተናግሯልና ሆኑ፤
እርሱ አዘዘም ፀኑም ይለናል።
በመጀመሪያ ቃል ነበር በሚለው ዐረፍተ ነገር የሚጀምረው የዮሐንስ ወንጌልና በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይና ምድርን ፈጠረ ከሚለው የዘፍጥረት መጽሐፍ የመጀመሪያ ቃል ጋር ያለምክንያት እንደአልተመሳሰለ ልብ ልንል ይገባል። ይሕ የእግዚአብሔር ቃል ከፍጥረት በፊት ሕልው ነበር። የእግዚአብሔርን ከአንድ በላይነት ሲነግረን" ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበር" ብሎ ይለንና ሕብረታቸውን ሲያፀናልን ደግሞ “ያም ቃል እግዚአብሔር ነበር” ይለናል። ስለዚህ ጌታ ወልድ ከአባትነት በቀር አብ የሆነውን ሁሉ፣ አብ አባትም ከልጅነት በቀር ወልድ የሆነውን ሁሉ ሆኗል። በብሉይ ኪዳን ኢሳይያስ "የእግዚአብሔርን መንገድ በምድረ በዳ ጥረጉ ለአምላካችንም ጎዳና በበረሃ አስተካክሉ" ሲል ማቴዎስ ደግሞ "የጌታን መንገድ አዘጋጁ ጥርጊያ ውንም አቅኑ" ይላል። ኢዮኤል "የእግዚአብሔርን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል" ሲለን ጳውሎስ "የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል" ብሎ ይተባበራል። ዘካርያስ "አምላካችን እግዚአብሔር ከቅዱሳኑ ጋር ይመጣል" ብሎ ሲል ተሰሎንቄ ላይ ጳውሎስ "ጌታ ከቅዱሳኑ ሁሉ ጋር ሲመጣ" በማለት እግዚአብሔር በክርስቶስ ውስጥ ክርስቶስም በእግዚአብሔር ውስጥ እነደነበር ይፅፍልናል። ለዚሕም ነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአዲስ ኪዳን ውስጥ በመደጋገም "እኔና አብ አንድ ነን" ፣ "እኔን ያየ አብን አይቷል "፣ "እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ እመኑ" በማለት ስለማንነቱ ምስክርነት የሰጠን።
ሐዋርያው ዮሐንስ ከእኛ በፊት ኖረው ላለፉትም አሁን በዚህ ምድር ላለነውም፣ መሲሑ ዳግምእስኪመጣ ድረስ ለሚመጡትም "ሕይወት በእርሱ ነበረች፣ ሕይወትም የሰው ብርሐን ነበረች፣ ብርሐን በጨለማ ያበራ ነበር፣ ጨለማም አላሸነፈውም" በማለት አንድ የጋራ የሆነ የእምነት መነሻ ያስጨብጠናል። ፀሐፊው በዚሕኛው ወንጌሉ ውስጥ ብቻ ሕይወት የሚለውን ቃል አርባ ግዜ ተጠቅሟል። ለዚሕም ይመስላል ‘ሕይወት የሚገኘው በክርስቶስ ነው፣ጌታ ራሱ ሕይወት ነው፣ እኔ ሕይወት እንዲሆንላችሁ እንዲበዛላችሁ መጣሁ፣እግዚአብሔር የሰጠን የዘልዐለም ሕይወት በልጁ ውስጥ ይገኛል’ እያለ በመደጋገም በአፅንኦት የሚናገረው።
በዘፍጥረት መጽሐፍ መጀመሪያ ላይ ብርሐን ይሁን ሲል በጥልቁ ላይ የነበረውን ጨለማ የገሰፀው የእግዚአብሔር ቃል የሆነው ክርስቶስ ለጠፋነውና በፅልመት አለም ውስጥ ለነበርነው የሰው ልጆች ሁሉ ብርሐን ሊሆነን ከጨለማም ወደሚደነቅ ብርሀን ሊያፈልሰን እንደመጣ ፀሀፊው የምስራች ቃል ይነግረናል። ብርሀን ከሌለ ሕይወት የለም። ጌታ ክርስቶስ በዚሁ ወንጌል 8፥12 ላይ "እኔ የአለም ብርሃን ነኝ በእኔም የሚያምን ሁሉ የሕይወት ብርሃን አለው ጨለማም በእርሱ ዘንድ አቅም አልባ ነው" ይለናል። ፀሀፊው ብርሀን የሚለውን ቃል ሰላሳ ግዜ ጨለማ የሚለውን ቃል ደግሞ ዘጠኝ ግዜ ያህል በመጠቀም ብርሀን በሆነው በክርስቶስ በማመናችን እግዚአብሔርን ማን እንደሆነ ማወቅ መቻል ብቻ ሳይሆን የሐጢዐት ጨለማችንንም ማሸነፍ እንደቻልን ይነግረናል። ዮሐንስ ከላይ ጌታ፣ አምላክ፣ ፈጣሪ፣ብርሃን፣ሕይወት፣ ነፃ አውጪ፣የእግዚአብሔር ቃል ሲል ያስተዋወቀውን ክርስቶስ "ቃልም ስጋ ሆነ ፀጋንና እውነትንም ተሞልቶ በእኛ አደረ&" ሲል በአስገራሚ መገለጥ ያሳየናል። በዕብራይስጥ ቋንቋ ፀጋና እውነት ሁልጊዜም የሚተረጎሙት የማይለወጥ ፍቅርና ታማኝነት ተብለው ነው። በዚህ ስፍራ የእግዚአብሔር አምላክ የጠፉትን የሰው ልጆች ማዳን መፈለጉና ውዴታው ራሱ የፈጠረውን የሰውን ስጋ ለብሶ ዝቅ እስከማለት ድረስ እንደነበር እንረዳለን። ስጋ (ትስጉት) የሚለው ቃል በዚህ ስፍራ የተገለጠው ጌታችን ከኃጢአት በስተቀር የሰውን ሁለንተናዊ ማንነት እንደለበሰ የሚገልጽ ሆኖ ነው። ጌታችን ክርስቶስ ሰዎችን በወከለ ሁለንተናዊ ማንነት ቢገለፅም ከርሱ በፊት ማንም ፍጡር ያልነበረውን ፀጋንና እውነትን የተሞላ ሆኖ በመካከላችን ማደሩ ጌታን የተለየ አድርጎታል። በጥቅሉ ሲታይ እግዚአብሔር ከሐጢዐት በፊት የፈጠረውን ትክክለኛና እንከን አልባ ሰው ምሳሌ ለሰው ልጅ ሁሉ የገለፀው አንድያ ልጁን ስጋ በማልበስ መሆኑ ነው።
ዮሐንሥ በዚሕ ምዕራፍ የሚያነሳው ታላቁና ሁለተኛው የእግዚብሔር አላማ በክርስቶስ ኢየሱስ በሆነው የማዳን ሥራ ሰውን ለመታደግ እንዲሁ በፀጋው መወሰኑን ነው። ጳውሎስ ለኤፌሶን ቤተክርስቲያን በፃፈው መልዕክቱ ላይ "በሰማይ መንፈሳዊ በረከትን በመስጠት በክርስቶስ ባረከን" ብሎ እንደሚለው የእግዚአብሔር አምላክ ለሰው ልጆች የሰጠው ቀዳሚ የፀጋ ስጦታው ራሱ ጌታ ክርስቶስ ነው።ይሕ ፀጋ እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ሁሉ ያሳየው ጥልቅ ፍቅሩና ምሕረቱ ምሳሌ ነው። ምንም እንኳን ሰው የእግዚአብሔርን ፍቅርና ምሕረትን ማግኘት የማይገባው ሆኖ በከፋ ኃጢአት የነበረ ቢሆንም ከፀጋው የተነሳ ደሕንነትን አግኝቶ የዘለአለም ሕይወትን ይወርስ ዘንድ ስለወደደ ፈቃዱን በክርስቶስ ኢየሱስ አደረገ። አሜን!
* * *
"እንዳትወደኝ በመልካምነቴ...
ይሕ አይደለም ማንነቴ
እንዳትጠላኝ ደግሞ በጥፋቴ...
ፍቅር ነህ አያስችልህም አባቴ
ያለምክንያት ወደህ በምክንያት አትጠላም...
ለምህረትህ ስፍር መለኪያ የለውም
ያንተ ፍቅር መነሻው ከራስህ
የመውደድ ልብ የማያልቅብህ የኔ ጌታ።"
(ከሐና ተክሌ መዝሙር የተወሰደ)
በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 3፥ከቁጥር 16-18 በጌታ ያመንን ቅዱሳን ሁሉ ብንጠየቅ ያለመሳሳት በቃላችን ልንወርደው
የምንችለው ተወዳጅ ጥቅስ እንዲህ ይነበባል፦
"በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘልዐለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ
ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና። ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና።
በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል።"
ይህ ጥቅስ እግዚአብሔር አምላክ ከፍጥረት እስከ ራዕይ ያሉትን የመፃህፍቱን ቃል፣ አላማውን፣ እቅዱን፣ ቃልኪዳኑን፣ የዘልዐለም ሀሳቡን፣ ፍቅሩን፣ ርህራሄውን፣ ምሕረቱንና የማዳን ፀጋውን በምልዐት የገለፀበት ትንሹ መፅሐፍ ቅዱስ ነው። ይሕ ጥቅስ በውስጡ ከተገለጸው ከእግዚአብሔር የፍቅር ጥልቀት የተነሳ ደጋግመን ባነበብነው ቁጥር የአምላካችንን ርህራሄና ፍቅር እንኳን ባመነው ቀርቶ በማያምኑቱ ልብ ዘንድ እግዚአብሔር ይወደኛል ያስብልኛልም የሚል ተስፋ መጫር የሚችል አቅም ያለው የእግዚአብሔር ቃል ነው። ስጋ ለባሽ በእግዚአብሔር ፊት እንዴት ጻድቅ ሊሆን ይችላል? ሲል ኢዮብ ጠይቆ እንደነበረው በአዳምና በሔዋን መኖርያ በኤደን ገነት ውስጥ አለማመንና ውሸት ተጋብተው ሁሉንም ሀጢዐቶች በወለዱ ግዜ አዳም ተባብሯቸው ነበር። በተቀደሰው በእግዚአብሔር ፊት በንፅህና ይወጣና ይገባ የነበረው አዳም ከስርዓት አፈንግጦ በመውጣቱ ከአምላኩ የሚለየው ቀውስ ተፈጠረ። በዚሕ መተላለፍ ምክንያትም ሞትን ጨምሮ ክፉ ነገሮች ሁሉ የሰው ልጆች ገንዘብ ሆኑ። የጌታ የእግዚአብሔር አምላክ ክብር በምልዐት በሚገኝበት ስፍራ ክፋትና ሐጢዐት ይኖሩ ዘንድ አቅም የላቸውምና አዳምና ሔዋን ከኤደን ገነት ይባረሩ ዘንድም ግድ ሆነ። የእግዚአብሔርም ቅድስና የዚህ አለምና የሰው ልጆች ሁሉ ሀጢዐትና መተላለፍ መለኪያ ጌጅ ሆነ። ሰው ምንም ቢያደርግ ፈጣሪን ደስ ማሰኘት እንዳይችል ሆኖ አቅም አጣ። ሁሉም ሀጢዐትን ሰርተዋል የእግዚአብሔርም ክብር ጎሏቸዋል ተብለን ስለተፈረደብን በበደላችንና በሀጢዐታችን ሙታን ሆነን ተገኘን። ከእርሱ ጋር መታረቅ እንችል ዘንድ ስድስ መቶ አስራ ሶስት ሕግጋቶችም ተሰጡን። እንደ አለመታደል ሆኖ ማንም ፈፅሟቸው አምላክን ደስ ማሰኘት ሳይችል ቀረ። የምናደርገው ነገር፣ የምንኖረው ኑሮ፣ የምንሰዋው መስዋዕት ሁሉ በአምላካችን ፊት ሁሌም ህፀፅ ነበረው። በመጨረሻ ቅዱስ እግዚአብሔር የገዛ ክንዱ ማዳንን ያመጣለት ዘንድ አንድያ ልጁን ክርስቶስን እርሱን ደስ ያሰኘ ወደ አምላካችን የቀረበ ዘመናችንንም ከውድቀት በፊት ወደነበረው ዘመን ያደሰ መስዋዕት አድርጎ ሰጠን። ዮሐንስ በዚህ ስፍራ የአምላካችን የእግዚአብሔር ፍቅር (ፀሐፊው በዚህ ወንጌል ብቻ ፍቅር የሚለውን ቃል 35 ግዜ ያሕል ተጠቅሟል) ለሰው ልጆች የተገለጠው ሰዎች ሁሉ በክርስቶስ ኢየሱስ በማመን ይድኑ ዘንድ ነው እያለን ነው። ይህንን ታላቅ ስጦታ የተቀበልነው ገፀ በረከት ሰጥተን ወይም የተቀደሰ መስዋዕት አቅርበን አልነበረም እንዲሁ በነፃ ከስጦታዎች ሁሉ የላቀውን ስጦታ እንቀበል ዘንድ ጌታአምላክ ስለወደደ እንጂ። እኛ በሀጢዐት የነበርነው የሰው ልጆች በእግዚአብሔር ቅድስና ፊት ልክ ሁነን የተገኘነው በወንጌል በተገለፀው ክርስቶስ አዳኝነት አምነን በመገኘታችን ነው። ፍፁም የሆነው መጥቶ ፍጹማን ሊያደርገንና ለመንግሥቱ ሊለየን ዋጋ ከፈለ። የፍቅርን ፅዋ ተጠምተን ነበር። የሀጢዐትና የሰይጣን ባሪያዎች ነበርን የአምላካችን ቤተሰብ አልነበርንም። የጠፋነውን ለመመለስ የወደቅነውን ለማንሳት የኦሪት ሕግ ስላልቻለ። ለሙታኖች ሞቶ በምክንያትላይጠላን ያለምክንያትም ሊወደን ፈቃዱ ሆኖ ተወዳጁ ጌታ ክርስቶስ መጣ። በርሱ ካመንን የእግዚአብሔር ልጆች መባል እንችል ዘንድ ክርስቶስ የሕግ ፍፃሜና ሕግን ፈፃሚ ሆነ። በጥቅሉ ሐዋርያው ዮሐንስ ይሕንን ይለናል። እግዚአብሔር ፍቅር ነው፣ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ታላቅ ስጦታ ነው፣ በእርሱ በማመን ብቻ ሰዎች ሁሉ የዘልዐለምን ሕይወት ያገኛሉ፤ ኢየሱስ ወደ አለም የመጣው በአለም ላይ ለመፍረድ ሳይሆን አለምን ለማዳን ነው፤ በዚህ በእግዚአብሔር ልጅ አዳኝነት አለማመን ፍፃሜው የዘልዐለም ሞት ፍርድ ነው እያለን ነው። ጳውሎስ 2ኛ ጢሞቴዎስ ምዕራፍ 1 ቁጥር 12 ላይ እንደሚለው አለመጥፋትንና ኢመዋቲነትን በክርስቶስ ወደ ብርሐን ያመጣው እግዚአብሔር ለዘለዓለም የተመሠገነ ይሁን፤ አሜን!
Comments