በመፅሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ በቃል ኪዳኖች ከተሞሉት ምዕራፋት አንዱ የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ አስራ አራት ነው። ሁሉንም ትተው
ይከተሉት ዘንድ የጠራቸው ጌታ የመጣበት ተልዕኮ ወደ ፍፃሜ እየደረሰ ከነርሱ ተለይቶ የሚሄድበትም አስጨናቂው ግዜ እየቀረበ በመጣበትና ተከታዮቹ መታወክ በጀመሩበት ሰዓት በእግዚአብሔር አባትና በልጁ በክርስቶስ ማመን ለታወከ ልብ እረፍት የሚገኝበት እንደሆነ ጌታ አትታወኩ በእግዚአብሔር እመኑ በእኔም ደግሞ እመኑ እኔ ከሚያልፈው ግዜና ክስተት ጋር አላልፍም ይልቁንስ ወደ አብ እሔዳለሁ መኖሪያም አዘጋጅላችኋለሁ ዳግም ተመልሼ (ይሕ ቃል ዳግም ተመልሶ ስለሚመጣበት ስለ ምጽአቱ የተነገረ ነው) እኔ ባለሁበት ትሆኑ ዘንድ እወስዳችኋለሁ ይላቸዋል።
የራዕይ መፅሐፍ ፀሐፊ የሆነው ይኸው ዮሐንስ በግዞት በፍጥሞ ደሴት በነበረበት ግዜ በተቀበለው "በጌታ ቀን በመንፈስ ነበርሁ" ብሎ በሚጀምረው የራዕዩ መፅሐፍ ምዕራፍ ሀያ አንድና ሃያ ሁለት ላይ ጌታችን ለእኛ ለልጆቹ ስለሚያዘጋጃት ከተማ ሲፅፍልን "መብራቷ በጉ ነውና በፊቱ ፀሐይና ጨረቃ ድምቀት ያጣሉ፣ በርሱ ከተማ ሌሊት የለምና በሮቿ ስለማይደፈሩ ሌባ ወይም ቀማኛ ዘልቆ አይገባባትም፣ ከመቀደሷና ከንፅህናዋ ልቀት የተነሳ ርኩሰትና ውሸት ይገኙ ዘንድ አቅም የላቸውም፣ የታነፀችው በራሱ በአምላካችን ነውና የሰው እጅ ስራ ስለሌለባት ውብ ናት፣ በአደባባይዋም ከእግዚአብሔርና ከበጉ ዙፋን የሚወጣ የሚያንፀባርቅ የሕይወት ውሃ ወንዝ ይፈስባታል፣ በዳርቻውም በበጋና በክረምት ያልተገደበ ፍሬን የሚያፈራ ቅጠሎቹ ለፈውስ የሚሆኑ ዛፍ አለባት ይለናል። በቀጣዩ ቃልኪዳኑ ደግሞ ሰውና መለኮት ሆኖ በመካከላችን የተገለጠው ጌታ እኔ መንገድም እውነትም ሕይወትም ነኝ ይላል። ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የመግቢያ መንገድን የሚያሳይ ብቻ ሳይሆን ራሱ መንገዱ፣ የእውነት መምሕር ብቻ ሳይሆን ራሱ እውነት፣ ሕይወትን የሚሰጥ ብቻ ሳይሆን ሕይወት በርሱ የነበረች ራሱ ሕይወት እንደሆነ ይናገራል። ሌላው የከበረው ቃልኪዳን ወላጆች እንደ ሌላቸው ልጆች የማንተው ስለመሆናችን የተነገረው ነው። እግዚአብሔር አምላክ አባታችን ነው በገላትያ መልዕክት "በእምነት በኩል ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁ" እንደሚል የስጋችንንና የልቦናችንን ፈቃድ እያደረግን በመኖር የቁጣ ልጆች የነበርነውን በመስቀል ገድል ዳግም ከማይጠፋ ዘር በመስቀል ገድሉ ታድጎን ለርስቱ የተለየን ወገኖች አደረገን። በአባቱም ዘንድ የታመነ ምሕረት ሆነልን። በብሉይ ኪዳን ዘመን "በእስራኤላውያን መካከል እኖራለሁ ሕዝቤን እስራኤልን አልተወውም" ብሎ ያለው ይሔ ምሕረት የሆነልን ጌታ በዚህ ዘመን በርሱ እስካመንን ድረስ እንደማይተወንና እንደማይረሳን ዳግም ያስረግጥልናል። በእግዚብሔር አለመረሳትና አለመተው ምንኛ ታላቅ እዳሎት ነው! ሌላው ቃልኪዳን የእምነታችን ራስ የሆነው ጌታ "በመንፈሱ ሰማያት ውበትን አገኙ፣ የእግዚአብሔር መንፈስ ፈጠረኝ ሁሉን የሚችል
አምላክም እስትንፋስና ሕይወትን ሰጠኝ" ሲል ኢዮብ የተናገረለትን፤ "ቅዱሱን መንፈስህን ከእኔ ላይ አትውሰድብኝ። መንፈስህን ትልካለህ ይፈጠራሉም፣ የምድርንም ፊት ታድሳለህ፣ በእግዚአብሔር ቃል ሰማያት ፀኑ ሠራዊታቸውም በአፉ እስትንፋስ" ሲል ዳዊት በመዝሙሩ ደጋግሞ የተቀኘለትን፤ "አንድ አካል አንድ መንፈስ አለ" "አሕዛብ በመንፈስ ቅዱስ የተቀደሱና እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ መስዋዕት ሆነው እንዲቀርቡ አገለግላለሁ" "የመንፈሱን ዋስትና በልባችን ያኖረ እርሱ ነው" በማለት ጳውሎስ የመሰከረለትን ቅዱስ መንፈስ በእኛ ሕይወት ውስጥ ይኖር ዘንድ ፈቃዱ መሆኑን ለእኛ ለተከታዮቹ ቃል ኪዳን የገባበት የተስፋ ቃል ነው።እግዚአብሔር የሆነው በፍጥረት ላይ የራሱ ድርሻ የነበረው ቅዱሱ መንፈስ ለእኛ ለአማኞች የተሰጠበት ዋንኛ አላማ በክርስቶስ የተጀመረውን ታላቁን የማዳን ተልዕኮ ወደ ፍጻሜ ማድረስና ስለ ጌታ ኢየሱስ እየመሰከረ አማኞች ወደ እርሱ ሙላት እናድግ ዘንድ ማገዝ እንዲሁም ክርስቶስ ደቀ መዛሙርትን እንደ አነቃቃቸው፣እንደ አበረታታቸውና እንደ አፅናናቸው ሌላ አፅናኝ የተባለው ጌታ መንፈስም በአማኞች ሕይወትና ኑሮ ውስጥ ይሕንኑ እንዲያረግ ነው። ዛሬ በእኛ ሕይወት ውስጥ ያለው መንፈሳዊ ዕውቀታችን፣ ደስታችን፣ ፍቅራችን፣ሰላማዊ ሕይወታችንና ምድራዊና ሰማያዊ ባርኮታችን ሁሉ ምንጭ የእግዚአብሔር አብና የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ የሆነው ቅዱሱ መንፈስ በእኛ ውስጥ መገኘቱ ነው። የዚህ የከበረ የዕውነት መንፈስ በእኛ ውስጥ መኖር ከዚህ ምድር ኑሮና ሕይወት ጋር የማያልፍ ይልቁንም ዘልዐለማዊ መሆኑ ሌላው በጌታ ያገኘነው ታላቅ ዕዳሎትም ጭምር መሆኑ ነው ልብና መንፈሳችንን በሀሴት እየሞላ ሐሌ ሉያ እንድንል ያደረገን።
Comments