top of page
Search
Writer's pictureወንድም አሰፋ ገብሩ

የማርቆስ ወንጌል የምንባብ ማስታወሻ፦ ከምዕራፍ 1 እስከ 5

ይህንን ወንጌል የሚፅፍልን ማርቆስ ምንም እንኳን ከማቴዎስ ወንጌል ጋር የሀሳቡ ፍሰትና ትረካው እጅግ የተቀራረበ ቢሆንም በጥንቃቄ ከታየ ወንጌሉ በአፅንኦት ትኩረት ያደረገው በጌታ አገልግሎትና ትምህርቶች ላይ ነው (ፓስተር መልኬ ስለአራቱ የአዲስ ኪዳን ወንጌላት ጥቂት ሐሳቦች በሚል ርዕስ ስር የፃፈውን መመልከት ጥሩ ግንዛቤ ይሰጣል)።


ምዕራፍ 1፥1-15፦ ሕግጋትንና ፅድቅን ሁሉ ለመፈጸም የመጣው ጌታ ኢየሱስ በዮሐንስ እጅ በተጠመቀበት ቅፅበት ልዩ እንደሆነ፣ ጌታ ለሰው ልጆች ሁሉ ቤዛ ይሆን ዘንድ እንደመጣ፣ እግዚአብሔር ደስ የሚሰኝበት ልጁ እንደሆነ ራሱ የእግዚአብሔር መንፈስ ከሰማያት ወርዶ ምስክርነቱን በመስጠት የጌታን የአገልግሎት ጅማሬ አብስሯል። ወዲያውም በሰይጣን ይፈተን ዘንድ መንፈስ ወደ በረሃ እንደወሰደው በነቢያት እንደተነገረው የጌታ መምጣት ለሰው ልጆች አርነት እንደሚሆን ያውቅ የነበረው ክፉ ጌታን ለአርባ ቀናት እንደፈተነው ኢየሱስም የእግዚአብሔርን ቃል በመጥቀስ እንደረታው እናነባለን። እኛም በዚህ በእኛ ዘመን በጌታ መንፈስና በጌታ ቃል መሞላት ጠቃሚ እንደሆነ ከራሱ ከጌታ እንድንማር ምሳሌ ሆኖልናል። ከቁጥር 16-28 ጌታ በወንጌሉ ዋነኛ ተልዕኮ ላይ የሚያግዙትን ሐዋርያት መምረጡን "ከአሳ ማጥመድ ይልቅ የከበረ ሽልማት ያለውን ሰዎችን አጥማጆች አደርጋችኋለሁ" እንዳላቸውና ሁሉንም ትተው እንደተከተሉት ያስነብበናል። የእለት ምግባቸውን ለማግኘት በገሊላ ባሕር ዳርቻ መረባቸውን ጥለው የሚጠብቁ ድሆችና ተሰፈኞች የነበሩትን ሰዎች መንግስቱን በመመስረት ስራ ላይ ግምባር ቀደም ሰራተኞች ይሆኑ ዘንድ መረጠ። "ኑ ከእንግዲህ ሰዎችን አጥማጆች አደርጋችኋለሁ" አላቸው፤ እነርሱም መረባቸውን ትተው ተከተሉት። እሺ ብለን እንታዘዘው እንጂ ጌታ ሲጠራ እሱ ከውልደት ጀምሮ የሰጠንን የተፈጥሮ ክህሎታችንን ሳይቀር ለመንግሥቱ ጠቃሚ ማድረግን ያውቅበታል። ከቁጥር 29-45 የእግዚአብሔር ርህራሄ በጌታ ኢየሱስ እጆች በኩል ለሰዎች እንዴት እንደተገለጠና በንዳድና በለምፅ የተመቱትንና በአጋንንት የታሰሩትን ሁሉ ነፃ እንዳወጣ እናነባለን።በዚህ ስፍራ በጣም አስደናቂው ክንውን ሆኖ የተገኘው ጌታ በምኩራብ ሲያስተምር መፃህፍትን ጠንቅቀው የሚያውቁት ምሁራን በጉባኤቸው ከአጋንንት ጋር አብረው መቀመጣቸውን እንኳን አለማወቃቸው ብቻ ሳይሆን ጌታን ከእነሱ ይልቅ ቀድሞ ማን እንደሆነ የለየውና ማንነቱንም ጭምር አውቆ "ማን እንደሆንክ አውቄያለሁ የእግዚአብሔር ቅዱስ" ብሎ መመስከሩ ነው።


በምዕራፍ 2፥1-12 ኢየሱስ ሽባውን ሰው እንደፈወሰው እናነባለን። በዚህ ስፍራ ምንም እንኳን ተሸክመው ያመጡት ሰዎችና የሽባው ሰው ፈውስን የመሻቱ ፅናት የሚያስደንቅ ቢሆንም ጌታ ከአካሉ ፈውስ በፊት "ሀጢዓትህ ተፈወሰችልህ" በማለት ነው ነፍሱን የፈወሰለት። ጻፎችም ይሄ ማነው የኃጢአት ስርየት የሚሰጥ በማለት ሲያጉረመርሙ" በስጋው መፈወስ ቀላል ጉዳይ ነው እሱ የሚያስፈልገው የስርየት ፈውስ ነው። የስጋውም ቢሆን አይቀርበትም ብሎ አልጋህን ተሸክመህ ሒድ አለው። ከቁጥር 13-17 ጌታ የእልፍዮስን ልጅ ሌዊን ወይንም ማቴዎስን ጠራው (ጌታ ስምዖንን ጴጥሮስ እንዳለው ሌዊንም ማቴዎስ ብሎታል ተብሎ ይታመናል፤ የስሙ ትርጉሙም የእግዚአብሔር ስጦታ ማለት ነው)። ሌዊም እንደ ሌሎቹ ሐዋርያት ሁሉንም ትቶ ተከተለው። ማቴዎስ ጌታን ሳይፈልግ ጌታ ፈለገው።የጌታ የመጥራቱ ፀጋ ፅንፍ የለሽ፣ ርህራሄውና ምሕረቱ ማለቂያ የሌለው፣ እንደ ሰው መተላለፋችን ሳይሆን ነፍሳችንንየሚፈልግ እንደሆነ ጥሩ ግንዛቤ ይሰጠናል።ማቴዎስ ከኃጢአቱ ተፈወሶ የታመነ የጌታ ወንጌል አገልጋይ ብቻ ሳይሆ የአረማይክና የግሪክ ቋንቋዎችን አጥርቶ መናገር መቻሉ ለጌታችን ወንጌል አገልግሎት ጠቃሚ ሰው ሆኖ ይገኝ ዘንድ አስችሎታል። ሌዊ በቤቱ ለጌታ ማዕድ ባዘጋጀ ግዜ ብዙ ሀጢያተኞችና ቀራጮች ተሰብስበው ስለነበር ይሔ መሲሕ ነኝ የሚል ሰው እንዴት ከእነዚህ ጋር መዐድ ይቀመጣል ባሉት ግዜ ለሚሰሙ ሁሉ "ሕመምተኞች እንጂ ብርቱዎች ባለ መድሀኒት አያስፈልጋቸውም ሀጢዓተኞችን እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁም" በማለት እግዚአብሔር መሪ የሚሆንበት አዲስ የአማኞች መንግሥት ለመመስረት የመጣበትን የታላቁን ተልዕኮ ምስጢር ይፋ አድርጎታል።


ምዕራፍ 3፥1-12 ፈሪሳውያን በዘፀዓት 31፥14-17 የተሰጠውን ሕግ መነሻ በማድረግ የሰንበትን ሕግ ሽሮአል፣ ከቀራጮችና ከሀጥዓን ጋር መዐድ ተቀምጧል፣ የኃጢአት ስርየት እሰጣለሁ በማለት የእግዚአብሔርን ብቸኛ ስልጣን ተጋፍቷል በተጨማሪም በብዙ ሰዎች ዘንድ መወደድና ተቀባይነትን በማግኘቱ በአይሁዳውያን ዘንድ የነበረንን ተሰሚነት እንድናጣ ሊያደርገን ይችላል በሚል

ሊከሱት ማሴር መጀመራቸውን ያስነብበናል። ከ13-19 የመረጣቸውን 12ቱን ሐዋርያት በአጋንንት ላይ ሳይቀር ስልጣን ሰጥቶ ሕመምተኞችን እንዲፈውሱ የምስራቹን ቃል ለሰዎች ሁሉ እንዲሰብኩ ለአገልግሎት ሾሟቸዋል። ከእርሱ ጋር እንዲኖሩ እርሱንም እንዲከተሉ ይነግራቸዋል። ከቁጥር 20-35 ኢየሱስ ያለ ምንም እረፍት አጋንንትን እያስወጣ ሕሙማንን እየፈወሰ በነበረበት ጊዜ ይህን የሚያደርገው በሰይጣን ሀይል ነው ብለውታል፤ ይሁን እንጂ ጌታ ኢየሱስ ከበሽታም ፈዋሽነቱ ባለፈ ሕዝብን ሁሉ ከኃጢአት ሊታደግ የመጣ የእግዚአብሔር ልጅ ነበር ዬሽዋ ለሚለው የዕብራይስጥ ቃል በግሪክ ኢየሱስ የሚል ፍቺ ሲኖረው ትርጓሜውም እግዚአብሔር ያድናል ማለት ነውና።


ምዕራፍ 4፥1-20 ጥበበኛው ኢየሱስ እንደ ሁልግዜው ትምህርቱ በሰዎች አእምሮ ውስጥ እንደማይረሳ ሆኖ ተስሎ ይቀመጥ ዘንድ በሰጠው የዘሪው ምሳሌ ግራ የተጋቡት ተከታዮቹ በጠየቁት ጊዜ ለእናንተ የአምላክን መንግሥት ምስጢር የማወቅ እዳሎት ተሰጥቷችኋል ይላቸዋል። ይህ ክፍል ለመረዳት አዳጋች ቢመስልም በምሳሌ የሚቀርበውን እውነት ለሚቀበሉ ልቦች ሁሌም አብርሆት፣ ግልጠት ወይንም ግሕደት ሲሆን የምሳሌውን እውነትነት ለማያምኑ ልቦች ደግሞ አስተውሎታቸውን የሚጋርድ ሆኖ ይገኛል። ስለዚህ ቃሉ መለኮታዊና ሐቅ መሆኑን ያለጥርጥር የተቀበሉ ልቦች በጥንቁቅ ገበሬ በማለፊያ መሬት ላይ እንደተዘራ ዘር ሲበቅልም ብዙ ፍሬ እንደሚሰጥ እንደዚያ ይሆናሉ። ከቁጥር 26-29 ያለውን ክፍል ያለውን የዘር ምሳሌ የምናገኘው በማርቆስ ወንጌል ውስጥ ብቻ ነው። ዘሪው ዘሩን ከሰጠው ከዘሩ ባለቤት ተቀብሎ ከዘራው በኋላ ለማደጉና ፍሬያማ ለመሆኑ የእርሱ አስተዋጽኦ የለበትም የእኛ የአማኞች ድርሻ ዝሩ ተብሎ የተሰጠንን የሕይወት ቃል መዝራትነው። እንድንዘራ፣ እንድንተክል፣ አንድናጠጣ ተጠርተናል የማሳደጉ ድርሻ ግን የእግዚአብሔር ነው። በዘመኑ መጨረሻ የመከሩ ጌታ ፍሬውን ሊያጭድና ሊሰበሰብ ይመጣል፤ መልካሙን ዘር ወደ ጎተራው ይከታል፣ ያላፈራውንና እንክርዳዱን ደግሞ ወደ እሳት ይጥለዋል።


ምዕራፍ 5 ከቁጥር 1 እስከ 43 ላይ ማርቆስ ጌታ በገሊላ ምድር ስላደረጋቸው ታላላቅ የፈውስ ተአምራቶች፣ በአጋንንት እስራት ተይዞ በመቃብር ይኖር ሰለነበረው ሰው ፈውስ፣ ለሞት ስለቀረበችው ብላቴና ፈውስና ከአስራ ሁለት አመታት ስቃይዋ ስለተፈወሰችው ሴት ይፅፍልናል። ከ1-20 በመቃብር የሚኖር፣ በሰንሰለትና በእግር ብረት የሚታሰር፣ ሰዎችን ከመጉዳት የማይመለስ፣ ርቃኑን የሚኖር፣ አካሉን በድንጋይ የሚቧጭር የርኩሳን መናፍስትን የጭካኔ ጥግ የሚያሳይ፣ የስቃዪ ጥልቀትና ጉዳት ለልብ የሚከብድ ሌጌዎን በሚባል አጋንንት የተያዘን (ሌጌዎን 6 ሺህ ያህል ጭፍራዎች አሉት ከዚህ የሰውየውን ሀይለኝነት መገመት ይቻላል) ሰው ጌታ እንዴት እንደፈወሰው ይነግረናል። ከቁጥር 25-44 ባለው ክፍል ማርቆስ እምነት እንዴት የእግዚአብሔርን ሀይል እንደሚቀሰቀስ ያስነብበናል። ይህች ሴት ወደ ጌታ ከመምጣቷ በፊት ብዙ ባለመድሃኒቶች ጋር ከመሔድ ባለፈ ጥሪቷን ጨርሳለች። ይህም ሆኖ ስቃይዋ በዛ እንጂ ፈውስን አላገኘችም ነበር። በከተማው ዝናውን የሰማችለት የፈውስ ጌታ እያለፈ እንደሆነ በሰማች ግዜ ለሌሎች ታማሚዎች ያደረገውን እንዲያደርግላት መጣች። ጌታ ግን በብዙ ሰዎች ተከቦ ነበር ስለዚህ በልቧ "የልብሱን ጫፍ የነካሁ እንደሆነ እፈወሳለሁ" ብላ በእምነት የልብሱን ጫፍ ነካች፤ ፈውስም ሆነላት። የእምነቷ ፅናት ጌታችን ሀይል ከእኔ ወጥቷል እስኪል ድረስ ያደረገ እምነት ነበር። ከዚህ ክንውን ከምንማራቸው ነገሮች አንዱ ኢየሱስ የሌለበት እምነት ብቻውን ምንም እንደማያደርግና እንድንፈወስ፣ እንድንድንና የጌታ ትሩፋት እንዲኖረን ከተፈለገ እምነታችንና የጌታ ሀይል በአንድነት መስራት እንዳለባቸው ማወቅ እንደሚገባን ነው።

31 views0 comments

Comments


bottom of page