የሮሜ መልዕክት የተፃፈው ጳውሎስ ከሐያ አመታት በላይ ከሆነው አገልግሎቱ በኋላ በወንጌል ዕውቀቱ፣ በክርስቶስ ፀጋና በዕድሜውም በስሎ በነበረበት የሕይወት ዘመኑ በ55 ዓ.ም አካባቢ በቆሮንቶስ ከተማ ነው ተብሎ ይታመናል። ምንም እንኳን የቆሮንቶስን፣የተሰሎንቄንና የገላትያን መልዕክቶች ከሮሜ መልዕክቱ በፊት የፃፋቸው ቢሆኑም የሮሜ መልዕክት በእምነት አስተምህሮው ከሌሎቹ መልዕክቶቹ ይልቅ ቀዳሚውን ስፍራ የያዘ ጠንካራ ደብዳቤ በመሆኑ ከሁሉም በፊት ይነበብ ዘንድ ምክንያት ሆኗል። ማርቲን ሉተር ስለ ሮሜ መፅሐፍ ሲናገር “ማንኛውም አማኝ ቃል በቃል ሊያውቀው የሚገባ የዕለት ተዕለት የነፍስ ምግብ ነው፤ ደጋግመን ባነበብነው ቁጥር የክርስትና ዕሴቱና የወንጌል መልዕክቱ እየላቀ መጣፈጡም እየጨመረ ይሔዳል ” ብሎ ይለናል። ፀሐፊው የሮሜ መልዕክቱ አስኳል ያደረገው ”ፅድቅ የሚገኘው በዕምነት”መሆኑን በመናገር ሲሆን የዚህ መልካም መልዕክት የምስራች ነጋሪና ባለቤት ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነና በእርሱ በማመን ለሚገኘው የኃጢአት ሥርየት ምክንያት የሆነው ይህ ወንጌል ደግሞ የእግዚአብሔር ስጦታ የሆነውን ፅድቅ የገለጠ ነው ብሎ በማለት ነው። ከዚህ ባለፈ ሐዋርያው ሐጢዐት፣ ደሕንነት፣ እምነት፣ ቤዛነት፣ ምህረትና ፍርድም ላይ ሳይቀር አትኩሮት በመስጠት ብዙ ከመጻፉ በላይ በዚህ መልዕክቱ ውስጥ የገላትያ፣የቆላስያስ የቆሮንቶስና የኤፌሶን መልዕክቶች የተፃፉበትን አላማዎች ከወዲሁ ግልጽ አድርጓል።
ምዕራፍ አንድ ‘የክርስቶስ ወንጌል በእምነት የተገኘ ጽድቅ ወንጌል ነው’። በዚህ ምዕራፍ የመጀመሪያ ቁጥሮች ሐዋርያው ጳውሎስ ራሱን ሲያስተዋውቅ “ሐዋርያ ሊሆን የተጠራ፣ የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ባርያ፣ ለእግዚአብሔር ወንጌልም የተለየ” በማለት ሲሆን ፀሀፊው በዋጋ የተገዛ፣በፈቃዱም ለገዥው ሁለንተናዊ ክብሩን የሰጠ፣ የእኔ የሚለው የሚመካበት ምንም ነገር የሌለው ይልቁንም ፍፁም እምነቱ የተመሰረተው በገዥው ላይ እንደሆነ ሲነግረን “ከፍተኛ ገዥዬ እግዚአብሔር መሪዬም ስለ ሐጢዐቴ ሞቶልኝ ነፃ ያወጣኝ ክርስቶስ መመሪያዬም የሰጠኝ ይሕ የተስፋ ወንጌል” ነው ብሎ በማለት ነው። ሐዋርያው በዚህኛው ምዕራፍ የተልዕኮው መሠረት ወንጌልን መስበክ እንደሆነ ይናገራል። ወንጌል የእግዚአብሔር ነው፣ ምንጩም እግዚአብሔር ነው፣ ፀሐፊውም እግዚአብሔር ነው ይለንና ይህ ወንጌል አምላኬ እግዚአብሔር በእርሱ ዘንድ የነበረውን ምስጢር በክርስቶስ ኢየሱስ ለእኔ የገለጠበት የምስራች ቃል ሲሆን በዚህ ወንጌል በማመን ለሚገኘው ደሕንነት የሚረዳውን የወንጌሉን ስራ ለመስራት በክርስቶስ ኢየሱስ የተጠራሁት ደግሞ እኔ ብቻ ሳልሆን በዚህ ወንጌል በማመን የክርስቶስ ኢየሱስ የሆናችሁትን እናንተ ቅዱሳንም ጭምር እንጂ ብሎ ይለናል። በእምነት ለሚገኘው የነፍስ ቅድስናና ጽድቅ ሕያው እንዲሆን ለሕግና ለሐጢዐት ደግሞ ምውት ይሆን ዘንድ ስላስቻለው የጌታችን ወንጌል ሐዋርያ እንድሆን ስለተጠራሁበት ወንጌል አላፍርም የዚህ ወንጌል ተልዕኮ ለማዳን ነውና ብሎ በማለት በድፍረት ይናገራል።
በዚያ ዘመን ሰዎች ወንጌልን የሚመለከቱት በአንድ መሲሕ ሳይሆን መሲሕ ነኝ ባለ፣ ሞቱም በሮማውያን ዘንድ አስከፊ በነበረና ወንጀለኛም ነው ተብሎ በሚታመን ሰው የተሰበከን ወንጌል መስበክና ክርስቲያንና የክርስቶስ ተከታይ መሆንን መናገር አሳፋሪና አደገኛ በነበረበት ወቅት ነው ጳውሎስ በድፍረት “የተጠራሁበት ይሕ ወንጌል ተራ ወሬና የሚያሳፍር ሳይሆን የሰው ልጆችን ከዘለዓለም ሞትና ከኃጢአት የተናጠቀ፣ የእግዘብሔርን ልጅነትን ተስፋ ያስወረሰ ለደሕንነትም ይበቁ ዘንድ ያስቻለ የእግዚአብሔር ሀይሉ ስለሆነ በሮሜ ላላችሁ ቅዱሳንም እሰብከው ዘንድ የምጓጓና የተዘጋጀሁም ፈቃደኛ ባለ እዳ ነኝ” ብሎ ያለው። ሐዋርያው ይህንኑ እስከ ሞቱ ድረስ በማድረጉም በሮምና በፊሊጲሲዮስ ለእስራት፣ በኤፌሶንና በቆሮንቶስ ለተሳልቆትና ለውርደት ይጋለጥ ዘንድ ምክንያት ቢሆንም በተከታታይ በፃፋቸው መልዕክቶቹ ላይ፦ ‘ለእኔ ረብ የነበረውን ሁሉ ስለ ክርስቶስ እንደጉዳት ቆጥሬዋለሁ! የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ሀይል ነው! እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን!’ በሚሉት ሀያል ጥቅሶች በአፅንኦት ለጥሪውና ለጠሪው ታማኝነቱን አስረግጦልን አልፏል።
ምዕራፍ አንድ ከቁጥር 18-32፦ በዚህ ክፍል በ1ኛ ቆሮ 1፥18 ላይ ጳውሎስ “የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ሐይል ነው” ብሎ ያለበትን ምክንያት ከወዲሁ በዚህ በሮሜ መልዕክቱ ለማስተዋወቅ እየተዘጋጀ እንዳለ እንረዳለን። የእግዚአብሔር ጽድቅ በወንጌል አማካኝነት እንደተገለጠው ሁሉ የእግዚአብሔር ቁጣም እግዚአብሔርን እንደ እግዚአብሔርነቱ መጠን ባልተቀበሉት ላይ የተገለጠው በዚሁ በጌታ ወንጌል ነው። የወንጌሉ ስራ ከሀጢዐት ነፃ አውጥቶ ለደህንነትና ለጽድቅ በማብቃት በእምነት የአምላካችን መንግሥት ወራሾች እንድንሆን ማስቻል ብቻ ሳይሆን በምድር ኑሮአችንም በየቀኑ በፅድቅ በመኖር አግዚአብሔርን ማክበር እንችል ዘንድ አቅም ሊሆነንም ጭምር ነው።ለዚህም ነው ነብዩ ዕንባቆም “ጻድቅ በእምነት ይኖራል” ያለው። ነገር ግን እንደ አለመታደል ሆኖ ብዙዎች በወንጌል ብቻ ሳይሆን በህላዌ አለምና በፍጥረትም ሁሉ ላይ በግልጥ የሚታየውን ይሕንን ታላቅ ስጦታን በመቀበል እግዚአብሔርን እንደ አምላክነቱ መጠን ዕውቅና ሊሰጡት ስላልፈለጉ የሚገባውን ክብር በመንፈግ ምርጫቸው የአምላክ የለሽነት መንገድና ሕይወት ስለሆነ፣ ከክፋታቸውም የተነሳ እውነትን አንቀው በመያዝ የእግዚአብ ሔርን ሕልውና ስለካዱ እግዚአብሔር ለሞኝነት ተጋልጠው ልባቸው እንዲጨልም፣ሀሳባቸውም ፍሬ አልባ ይሆን ዘንድ ለገዛ መሻታቸው ይተዋቸው ዘንድ ግድ ሆኗል። ከሰው ልጆች ሕይወት፣ከታሪክና ከከበረው የእግዚአብሔር ቃል እንደምንረዳው የሰዎችን ሕሊና እየቆነጠጠ በመገሰጽ ወደ እግዚአብሔር ሕልዎት ለማምጣት ብሎም ለንሰሐ ለማብቃት አቅም ያለውን የእግዚአብሔርን ማንነት ሆነ ብለው የሚክዱትን ሁሉ ሀይ የሚል ከልካይ የሌላቸው ሆነው በፈቃዳቸው ያሻቸውን ያደርጉ ዘንድ እግዚአብሔር ለማይረባ አእምሮ፣ለውሸት፣ ለሚያስነውር ምኞትና ገደብ የለሽ ለሆነና ተጠያቂነት ለሌበት የስጋና የነፍስ አመፃ አሳልፎ ሲሰጣቸው አይተናል። አሳልፎ ሰጣቸው የሚለው ቃል በዘመናችን ከወንጌሉ ቃል ያፈነገጠ ርዕዮት ባላቸው አብያተክርስቲያናትና ተከታዮቻቸው ዘንድ እግዚአብሔር የፍቅርና የይቅርታ አምላክ ስለሆነ ይህን ያህል ቁጡ ሆኖ ሰዎችን አሳልፎ አይቀጣም በማለት ከቃሉ ጋር የሚጣረስ ሀሳብም ስብከትም በማሰማት እየሞገቱን እንዳለ ይታወቃል። እግዚአብሔር በክርስቶስ የገለጠው ትልቁ አላማው ሰዎች ሁሉ በእምነት ጸድቀው ገንዘቦቹ ይሆኑ ዘንድ ነው ይሕም በእርግጠኛነትnሊታወቅ የሚገባው ሐቅ ነው። እንደ አለመታደል ሆኖ እግዚአብሔርን በማወቅ ሊታደስ ይገባው የነበረው አእምሮአቸው የማይረባ ነገር ስላሰበ ሀሳቡንም ወደ ድርጊት ስራ ቀየረ ከአምላካችን ጥበቃ ወጥተው ብቻቸውን በመሆን በሀጢዐታቸው ይቆዩ ዘንድ እግዚአብሔር ራሱን ከእነሱ በማራቅ ለክፉ አእምሮ ይጋለጡና በውጤቱም የዘሩትን ያጭዱ ዘንድ ትቷቸዋል። ሁላችንም በጌታ የሆንን አማኞች የማንክደውና ሊሰመርበት የተገባው ታላቁ እውነት እግዚአብሔር የበጎነት ሁሉ ባለቤት መልካምነትም የርሱ ገንዘቡና ማንነቱ መሆኑን እንደምናውቅ ብቻ ነው። ቃሉም የሚያስረግጥልን እግዚአብሔር መልካም በመከራም ቀን መሸሸጊያ ነው በማለት ነው። በጌታ ያመኑ ቅዱሳን የጌታ ንብረቶቹ የመንፈሱ ማደሪያ መቅደሶች፣ እንደ አንዲት ንፅህት ድንግልም ለክርስቶስ የታጩ (2ኛ ቆሮ 11) ሙሽሮች በመሆናቸው በአእምሮም፣ በሞራልና በስነምግባር በምንም አይነት ሁኔታ ከዚሕ ክልል ወጥተው ይሄዱ ዘንድ እግዚአብሔር ፈቃዱ አይደለም ነገር ግን በአመፃና በእንቢተኝነት የእርሱ ማደሪያ የሆነው ማንነታችውን ባቆሸሹ ግዜ የተቀደሰውን የጌታን መንፈስ ያሳዝናሉ። በዚሕም ምክንያት መንፈሱ ከነርሱ ጋር እንዳይቆይ ቅድስናው ስለሚከለክለው ነው እንጂ እግዚአብሔር ሰዎች በመተላለፍ ውሰጥ እንዲሆኑና ለኃጢአትም ተጋልጠው ዋጋ ይከፍሉ ዘንድ ፈቃዱ ስለሆነ አይደለም። ስለዚህ ሰዎች በዓመፃና በፈቃዳቸው ከእግዚአብሔር በተለዩ ግዜ ለዚህ አለም ገዥ ይጋለጣሉ ውጤቱም ከቁጥር 26-32 የተፃፈውይሆናል። ለማጠቃለል የእግዚአብሔር ቅድስና ባለበት ስፍራ ሁሉ ሐጢዐትና መተላለፍ ይኖሩ ዘንድ አቅም እንደሌላቸው ሁሉ ለእግዚአብሔርና ለተቀደሰው መንፈሱ ክብር በተነፈገበትም ስፍራ አይገኝ ዘንድ የእርሱ ማንነቱ ነው ከዚህ የተነሳም እኒህ ሰዎች ለበጎ ነገር ሊገዛና ሊታዘዝ የሚችል አእምሮ ስላጡ በኃጢአታቸው ምክንያት ከእግዚአብሔር ሕልዎት እየራቁ ሔዱ ለማይገባ ነገርና ለግልሙትና ራሳቸውን አሳልፈው በመስጠት ተባበሩ። ለዚህ ነው ሐዋርያው ጳውሎስ ‘የእግዚአብሔርን ክብር በፍጥረት በመተካታቸው ምክንያት የጠፉትን እነዚህን ሰዎች ለሶስት ግዜ ያሕል አሳልፎ ሰጣቸው’ ካለ በኋላ ‘ምሕረትን ያጡ ናቸው፤ እንደዚህ ለሚያደርጉትም ሞት ይገባቸዋል’ በማለት ምዕራፉን የደመደመው።
Comments