top of page
Search
Writer's pictureወንድም አሰፋ ገብሩ

የሐዋርያው ጳውሎስ መልዕክት ወደ ሮሜ ሠዎች ማስታወሻዎች፦ ክፍል ሦስት

ምዕራፍ ሰባት፦ ‘በክርስቶስ ከሕግ ተፋተናል’

በምዕራፍ ስድስት ላይ ፀጋ ስላለን እንዳሻን እንሁን የሚሉትን ይሔ የፀጋን ልቀትና የክርስቶስን መስዋዕትነት ማቃለል ነው ብሎ በመሞገት እፎይ ከማለቱ ሌሎች ፅንፈኞች ተነሱ። ተው እንፀድቅ ዘንድ ሕግን ጭምር መጠበቅ አለብን ማለት በመጀመራቸው ጳውሎስ ስለ ሕግ ደግሞ ለማብራራት ግድ ሆኖበታል። ይሕ ወንጌል ሳይበረዝ እኛ ጋ ይደርስ ዘንድ ይህ የእግዚአብሔር ሰው የከፈለው ዋጋ ምንኛ ታላቅ ነው!

ወንድሞች የሚለው ቃል የጳውሎስ ሀሳብ ያነጣጠረው በክርስቶስ ባመኑ ክርስቲያኖች ላይ እንደሆነ ያስረዳናል። በዚያ ዘመን በነበሩት ክርስቲያኖች ላይ የሕግ ጉዳይ ምን ያክል ክርስቲያንን እንዳናወጠ የምንረዳው ጳውሎስ ከሐዋርያት ሥራ ጀምሮ በአፅንኦት የሚናገርበት ጉዳይ መሆኑ ነው። እዚህ ላይ ብቻ ሕግ የሚለውን ቃል 23 ግዜ ተጠቅሞበታል። ባሏ ስለሞተባት ሴት ባነሳው ምሳሌ ሕግን ከእምነት ጋር ለመደባለቅ ለሞከሩት ሰዎች አንድ ሰው በሕግ ሊዳኝና ሊፈረድበት የሚችለው በሕይወት እስካለ ድረስ ወይንም ሕጉ ተቀባይነት ባለበት ክልል ውስጥ እስከኖረ ድረስ ብቻ ነው። ከሞተ በኋላ ሕጉ ያሻውን ቢያደርግ እርሱ አይሰማም አይለማም። ያገባች ይሕቺ ሴትም ለባሏም ሆነ ለትዳሯ ተጠያቂነቷ ባሏ በሕይወት እስካለ ድረስ ነው።ልክ እንደዚህ ከጌታ ጋር ሞተው በተነሱ በእምነትም በፀደቁ ቅዱስን ላይ ሕግ በምንም ሁኔታ ጉልበት የለውም በጌታ በማመናችን ከሕግ ጋር ያቆራኘን ሰንሰለት ተበጥሷል በማለት በእኛና በሕግ መካከል የነበረው ግንኙነት እንደፈረሰ ያስረዳል። ጳውሎስ በዚህ ስፍራ ሕጉ ለእናንተ ሞቷል አይለንም እናንተ ለሕግ ሞታችኋል እንጂ ስለዚህ በሕግ ልንፈረድ አይገባም፤ ልክ ባሏ እንደሞተባት ሴት በጌታ ገድል ከቀደመው ባላችን ነፃ ወጥተን ያለ ኩነኔ የክርስቶስ ሙሽሮች እንሆንለት ዘንድ ፀጋ ነፃ አውጥቶናል። ለጌታ መሞቱ እርግጠኛ በሆነ አማኝ ላይ ሕግ ይፈርድበት ዘንድ ሀይል የለውም።

ሐዋርያው ጳውሎስ የነፃነት ምዕራፍ ተብሎ በሚታወቀው በምዕራፍ ስምንት በክርስቶስ ኢየሱስ ያለነው ከሀጢአት ኩነኔ ነፃ መሆናችንናን ከክርስቶስ ፍቅር ሊለየን የሚችል አንዳች ሀይል እንደሌለ፤ በምዕራፍ ዘጠኝ፣ አስርና አስራ አንድ በእስራኤል አለማመን የተሰማውን ሐዘን ገልጾ የማይሻረው የእግዚአብሔር የተስፋ ቃል ለእስራኤል እንዳልታጠፈና አሁንም ገና ተስፋ እንዳለ፣ የእርሱ የልቡ ፈቃድም እስራኤል ይድኑ ዘንድ ብዙ ሐዘን የማያቋርጥም ጭንቀት እንዳለበትና ሰምተውት ራሳቸውን የሕግ ፍፃሜ ሁሉ ከእርሱ በእርሱና ለእርሱም ለሆነው ለክርስቶስ በመስጠት ይፀድቁ ዘንድ ያለውን ተማፅኖ፤ በምዕራፍ አስራ ሁለት፣አስራ ሶስትና አስራ አራት ደግሞ ክርስትናችንን በተግባር ለመግለፅ ይረዳን ዘንድ በሙሉ መሰጠት የሆነ እግዚአብሔርንም ደስ የሚያሰኝ ሕያውና ቅዱስ የሆነ የእኛነታችን መስዋዕት ለማቅረብ በአእምሮና በልብ መታደስ እንድንለወጥ፣ እርሱን ስናገለግል ደግሞ በመቀባበል በፍቅርና በባለ ዕዳነት መንፈስ ሳይሆን እንደ እዳሎት በሚቆጠር ደስታ ያለመታከት እንዲሆን፣ በተስፋ ደስ እንዲለን፣ በፀሎት እንድንፀና፣ እንግዶችን በመቀበል እንድንተጋ፣ የሚያሳድዱንን እንድንመርቅ፣ በመስማማት እንድንኖር፣ ለባለ ስልጣኖችmእንድንታዘዝ ያስተምረናል።

በምዕራፍ አስራ አምስት፦ ክርስቶስ በመካከላችን በነበረ ግዜ በብዙ ጉስቁልና እስከ መስቀል ሞት የሄደው ለእኛ እንጂ ለራሱ ደስታ አልነበረም። ስለዚህ ብርቱዎች ደካሞ ችን እንድንሸከም ይገባል። የምናደርገው ነገር ሁሉ ለጌታ ክብርን ያመጣ ዘንድ አንድነታችን ከልባችን ውስጥ መመንጨት እንደ አለበት ሲነግረን በአንድ ልብና በአንድ አፍ እግዚአብሔርን አክብሩ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ክብር እንደተቀበላችሁ እንዲሁ እርስ በእርሳችሁ ተቀባበሉ ይለናል። ምዕራፍ አስራ ስድስት የሐዋርያውን ባሕሪና ማንነት የሰብከውን ወንጌል እንዴት በምልዐት እንደሚኖረው ትሕትናው የሚያስገርም የመሪነት ብቃቱ የተዋጣለት ወገኖቹ ሲሳሳቱ በፍቅር የሚወቅሳቸውን ያሕል እንዴት ከልቡ እንደሚወዳቸው የገለፀበት ምዕራፍ ነው። በክርስቶስ የሚወዳቸውን፣የረዱትንና ነፍሳቸውን ለነፍሱ እስኪያቀርቡ ድረስ የደገፉትን፣ ክርስቶስን በማመን የቀደሙትን፣ በእምነታቸው ተፈትነው የተመሰገኑትንና አብረውት ያገለገሉትን ያየባቸውን ፀጋ በነቂስ በመውጣት እውቅና እየሰጠ ያበረታታቸዋል።

በማስታወሻችን መጨረሻ ሳናነሳ የማናልፈው 16፥25 ላይ ያለው “ወንጌሌ” የሚለው ቃል ነው። ጳውሎስ በጻፋቸው በሁሉም መልዕክቶቹ የእግዚአብሔርና የክርስቶስ ወንጌል ሲል ከቆየ በኋላ በዚህ ስፍራ ወንጌሌ (my gospel) በማለት ያስነብበናል። እንደአለመታደል ሆኖ ይሕ አባባሉ በጌታና በጳውሎስ ወንጌል መካከል የወንጌል ልዩነት ያለ እስኪመስል ድረስ ወደ ሌላ ፅንፍ ተለጥጦ የተወሰደበት ግዜ እንደነበር እናውቃለን። በአዲስ ኪዳን ወንጌል የሚለው ቃል ከሰባ ግዜ በላይ ጥቅም ላይ ሲውል ለሀያ ሰባት ግዜ የተጠቀመበት ደግሞ ጳውሎስ ነው። በዚህ ስፍራ ብቻ ነው ወንጌሌ ሲል የተነበበው። ወንጌሌ የሚለው ቃል በራሱ ምንጭ መሆንን ወይንም ባለቤትነትን ገላጭ መሆንን ለማመልከት ሲባል አይደለም እዚሕ ቦታ የተጠቀሰው። ይልቁንም ይህ ወንጌል ከጌታ የተቀበልኩትና እስከ ሞት ድረስ የታመንኩለት እኔነቴም የተሰራበት የማንነቴ መገለጫ ነው ከዚህ ውጪ በምንም አልታወቅም በሚል እድምታ እንጂ። ለዚህም ነው ወንጌሌ ከሚለው ቃል ተከትሎ የመጣው “ስለ ኢየሱስ ክርስቶስም እንደ ተሰበከ” የሚለው ሀይለ ቃል በራሱ ወደ የትም ዝንፍ እንዳንል ያደረገን። በማስታወሻዬ መጨረሻ ራሴን በጠየቅኩበት ጥያቄ ልለያችሁ። ጳውሎስ በሕይወት ኑሮ ለግላችን ወይንም ለቤተ ክርስቲያናችን ደብዳቤ ቢፅፍ ምን ይለን ነበር?

7 views0 comments

Comments


bottom of page