ከምዕራፍ 2 እስከ ምዕራፍ 5 ያሉት ቁጥሮች ስለ ጽድቅና ስለ ሕግ የሚናገሩና የሚያስተምሩ ምዕራፋት ሆነው እናገኛቸዋለን። ስለ አይሁዳውያን ጽድቅ ከ2፥1-3፥20፤ ስለ እግዚአብሔር ጽድቅ 3፥21-31፤ ስለ አብርሃምን ጽድቅ 4፥1-25፤ ስለ አማኞችን ድቅና
ውጤታቸው 5፥1-21 ውስጥ ሐዋርያው በዝርዝር አብራርቶልናል። ከአይሁድ ዘር የሆኑት ብሉይ ኪዳን ውስጥ በተሰጣቸው ሕግmትምከሕት ውስጥ በመግባት በእግዚአብሔር የተመረጥንና ሕጉንም የተቀበልን እኛ ከሌላው ዘር ሁሉ በጽድቅ የተሻልን ነን በማለት አረማውያንን በመናቅ ሀጥያተኞች ናቸው በማለት መፍረድ በመጀመራቸው ሐዋርያው ጳውሎስ ዋነኛው ጉዳይ ሕግን መቀበሉ ሳይሆን ሕግን መፈፀሙና መታዘዙ ነው፤ አረማውያን ሕግ ባይኖራቸውም በሕሊናቸው ስለሚዳኙ ለራሳቸው ሕግ ናቸው፤ እናንተ ግን አይሁዳውያን ብትባሉ ለትምክህት ይሆናችሁ ዘንድ በሕጉ ብትደገፉ ለሕጉ እስካልታዘዛችሁ ድረስ ሕጉ ራሱ ይፈርድባችኋል ይላቸዋል። ይሕን መታበያቸውን አስቀድሞ ያውቅ የነበረው ጌታ ነብዩ ሚክያስን (3፥11) “ፅዮንን በደም ኢየሩሳሌምንም በኃጢአት ይሰራሉ፣አለቆችዋም በጉቦ ይፈርዳሉ ካሕናቶቿም በዋጋ ያስተምራሉ ነቢያቶችዋም በገንዘብ ያሟርታሉ እግዚአብሔር በመካከላችን አይደለምን? ክፉ አይመጣብንም እያሉ በእግዚአብሔር ይታመናሉ” ብሎ ይናገር ዘንድ ያደረገው ያለ ምክንያት አልነበረም። በዚህ ስፍራ ልብ ልንለው የሚገባው በሙሴ ፅላት ሕግን የጻፈላቸው እግዚአብሔር በአረማውያን ልብና ሕሊና ላይ የተፈጥሮን ሕግ መጻፉን አይሁዳውያን ልብ አለማለታቸውንም ጭምር ነው። እነዚህ በወቅቱ የነበሩ አይሁዳውያን የሐይማኖትን ካባ ይልበሱ እንጂ የአምላክን ሀይል ግን ክደው ነበር። ለእግዚአብሔር ውዶቹ ስለሆን ሕግን መፈፀም አይጠበቅብንም አሉ። በዚሕ ድርጊታቸውም ሳቱ የእግዚአብሔር የጽድቅ ፍርድ ከሰው ልጆች ፍርድ በእጅጉ የተለየ መሆኑና ለዚህ መተላለፋቸው ዋጋ ከፋይ እንደሚሆኑም ጭምር ዘነጉ። ሐዋርያው ስለ አምላካችን ቅን ፈራጅነት ያሳሰበን፦ የእግዚአብሔር የፍርዱ ምንጭ ሰዎችን ወደ ንስሀ የሚመራው ቸርነቱ እንጂ እንደ ፍጥረት የበቀል ፍርድ አለመሆኑን ነው። ፍርዱ ለእያንዳንዱ እንደ ስራው በመሆኑ የፍርዱን መጠን የሚወስነው የእኛ ስራ እምነትና ከእግዚአብሔርና ከሕግጋቱ ጋር ያለን ዝምድናና ተጣምሮ ነው አይጨምርም አይቀንስም ጌታ እግዚአብሔር ሕፀፅ በሌለበት ትክክለኛ ፍርዱና ፈራጅነቱ የታወቀ ነውና ብሎ ይላል። የሰው ልጆች ፈራጅነት ዋንኛ መነሻ ራስን ትክክለኛ አድርጎ ከሚቆጥር ግብዝነት፣ የራስን መተላለፍና አለመብቃትን ካለማወቅና ብሎም የእግዚአብሔርን የትዕግስቱን ባለጠግነት መጠንና ቻይነቱን ካለመረዳት የሚመነጭ መሆኑን ነው። ስለሆነም ዳዊት በመዝሙር 81 እንደተቀኘው ለችግረኛውና ለምስኪኑ ጽድቅ ለድሆችና ለድሀ አደጎች ፍርድ እንድናደርግ እንጂ እንድንፈርድ ስላልተጠራን ከመኮነን በፊት ራሳችንን እንድንመረምር መተላለፎች እኛም ዘንድ ሊገኙ ስለሚችሉ ከኃጢአት ብቻ ሳይሆን ከከሳሽነትም መንፈስ ነፃ በሚያወጣው የክርስቶስ ደም ዘወትር ራሳችንን መሸፈን እንደሚገባ እናውቅ ዘንድ ነው ሐዋርያው በብርቱ እየጣረ ያለው።
በምዕራፍ ሦስት ላይ በቀደመው ምዕራፍ ሲወቅሳቸው የነበሩትን አይሁዳውያን የእናንተ ብልጫ የቀደማችሁ የእግዚአብሔር ቃል ተቀባዮች መሆናችሁ ነው ቢሆንም ይሕንን አደራ ተቀብላችሁ እግዚአብሔርን ማስደሰት ባለመቻላችሁ ከዚህ አደራ ጎድላችኋል፤ ይሁን እንጂ ይሕ የእናንተ መጉደል የጌታ የእግዚአብሔርን ታማኝነት አያስቀርም የእግዚአብሔር ጽድቅ፣ ቅድስና፣መልካምነቱና ዕውነተኛነቱ በሰዎች መተላለፍ ምክንያት ከፍና ዝቅ ስለማይል እርሱ ወደ እኛ ባሕሪ አይወርድም እኛ ግን ቃሉንና ሕጉን በማክበር እርሱ ወደሚሻው ማንነት ልናድግ ይገባል ይላቸዋል። ከቁጥር 21-31 ባለው ክፍል ምዕራፍ 1-17 ላይ በጥቂቱ የጀመረውን የእግዚአብሔር ጽድቅ ከእምነት ወደ እምነት በእርሱ ይገለጣል ያለበትን ሐሳብ ያብራራው በቀደመው የኦሪት ሕግና በነቢያት የተመሰከረለት የእግዚአብሔር ጽድቅ ያለ ሕግ ተገልጧል፤ እርሱም በጌታ በክርስቶስ በማመን የሚገኝ ጽድቅ ነው ብሎ በማለት ነው። እጅግ አስገራሚው ነገር በፅላት ላይ የተጻፈው የመዳን ሕግ እስራኤልንና የሰው ልጆችን መታደግ ሳይችል መቅረቱ ነው። ዛሬ ግን በሰዎች ልብ ላይ በክርስቶስ ኢየሱስ በቀለም ሳይሆን በማመን የተፃፈውና የማይደበዝዘው የጌታ ፀጋ በመሆኑ እርሱን የተቀበሉ ሁሉ በዚህ አዲስ ጽድቅ በእግዚአብሔር ዘንድ ጻድቃን መሆናቸው በቻ ሳይሆን ከአብ ዘንድ ኢየሱስ ለሰው ልጅ አይሁድ ይሁን አረማዊ በክርስቶስ እስካመነ ድረስ የተገረዘን ስለ እምነት ያልተገረዘንም በእምነት የሚያፀድቅ አምላክ ሆኖ መሰጠቱ ነው።
ምዕራፍ አራት ላይ ሐዋርያው ስለ አብራሐምና የመፅድቁ ምክንያት ያብራራል። ሁላችንም እንደምናውቀው አብራሐም ከሁሉ በፊት በእግዚአብሔር የተጠራ የአይሁዳውያን አባት ነው። አብርሃም እግዚአብሔርን በማመን አድርግ የተባለውን በማድረጉ ጽድቅ ሆኖ እንደተቆጠረለትም እናውቃለን።ጳውሎስ በዚህ ምዕራፍ እኛ የአብርሃም ልጆች ነን የእርሱም ጽድቅ ወራሾች ነን ብለው ለታበዩ አይሁዳውያን የአብርሃም ጽድቅ ጅማሬ ከመገረዝ የቀደመው እምነቱ ነው መገረዙ ለማመኑ መገለጫ የሆነ የቃልኪዳን ምልክት ነው እያለ ይሞግታቸዋል። በዚህ ብቻም አላበቃም በአብርሃም ዘመን የምትመኩበት ልትፈፅሙት ግን ያዳገታችሁ ሕግም ቢሆን አልነበረም የነበሩት አግዚአብሔር አብርሃምና እምነቱ ናቸው ስለዚህ ዛሬ ደህንነትና ጽድቅ የሰጠን ሕግ ሳይሆን አብርሃም በእግዚአብሔር እንዳመነ እኛም በክርስቶስ ኢየሱስ አዳኝነት ያለ ጥያቄ ማመናችን ነው ይላል።
በምዕራፍ አምስት በእምነት ከሆነው ጽድቅ ጋር ስላገኘናቸው ስጦታዎች ነው የምንማረው። በእምነት ከመፅደቃችን የተነሳ ሰላም፣ወደ ፀጋው መግባት፣ በእግዚአብሔር ክብር የመመካት ተስፋ፣ የመታረቅና የንጉስ ልጅነትን አግኝተናል። ቀድሞ በኃጢአት ምክንያት ፀበኞች ነበርን ከእግዚአብሔርም ጋር ሰላም አልነበረንም፤ አሁን ግን እንደ አመንን ፀደቅን እንደፀደቅንም ሰላምን አገኘን። ከእግዚአብሔር የሚሰጠው ሰላም አለም እንደሚሰጠው አይነት ሰላም አይደለም የጌታችን ሰላም በምንም ዐይነት ምድራዊ ሀይል የማይነጠቅ የሁለንተና ሰላም ነው ይሕ ፅድቅና ሰላም የእግዚአብሔርን ልጅ የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ሕይወት ዋጋ የጠየቀ ነው።ሐጥያትን ለመቃወም ወይም ለሕግ ለመታዘዝ ምንም አቅም የሌለን ደካሞች፣ ሐጢዐተኞችና ጠላቶቹ በነበርንበት ግዜ ክርስቶስ ለሐጢዐታችን በመሞት ለእግዚአብሔር ሕያዋን አደረገን። እግዚአብሔርን ከበደልንበት በደል ባለፈውና በክርስቶስ ከሆነው የፀጋው ስጦታ የተነሳ የንጉሥ ልጆች ወደ ንግስና ዙፋን ለመቅረብ ከልካይ እንደሌለባቸው ሁሉ እኛም በክርስቶስ ወደ እግዚአብሔር ክብር የመቅረብ የማያሳፍር ተስፋ ባለቤቶች ሆንን። የዚህ ተስፋ መሰረቱ ደግሞ እሰከ ዛሬ ድረስ ብለን ብለን በቃላት ልንገልጸው ያልቻልነውና እጃችንን በአፋችን ላይ ያስጫነን ከመጠን ሁሉ የበዛው የእግዚአብሔር ፀጋ ነው! የምዕራፍ ስድስትን ዋንኛ ሐሳብ የጠቀለለው “ከመጠን ይልቅ የበለጠው የእግዚአብሔር ፀጋ ይበዛ ዘንድ ምን እናድርግ?” ለሚለው ጥያቄ “ለኃጢአት ሞተን ለክርስቶስ ሕያዋን እንሁን” የሚል ምላሽ በመስጠት ነው። የፀጋ የቁም ትርጉሙ ሀብት፣ መልካም ሥጦታ፣ ቅባሎት፣ ዕድል ፈንታ፣ይቅርታ፣ ክብር፣ ሞገስ፣ ስርየት፣ የእግዚአብሔር አብሮነት፣ ያለ ዋጋ የተሰጠና የተደረገ የቸርነት ሥራ ተብሎ ይፈታል።
ፀጋ የሚለው ቃል ከዘፍጥረት 6፥8 ‘ኖሕ በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ አገኘ’ ከሚለው ጀምሮ እስከ ራዕይ 22፥21 ድረስ ለ170 ግዜ ያሕል ተጠቅሶ እናገኘዋለን። የእግዚአብሔር ፀጋ ጅማሬ ምክንያቱ ምንድን ነው? ከተባለ በኃጢአት ምክንያት ከእግዚአብሔር አብሮነት የጎደለውን የሰውን ልጅ በክርስቶስ ኢየሱስ ቤዛነት አማካኝነት የዘልዐለምን ሕይወት ለመስጠት ሲሆን ጌታ የመጣው ደግሞ የሀጢዐት ስርየት መስዋዕት ለመሆን ብቻ ሳይሆን እርሱ በሰጠን ፀጋ በሀጢዐት ላይ የበላይ ሆነን እንኖር ዘንድም ለማስቻል ነው። የእግዚአብሔር ፀጋ ከመጠን ሁሉ በለጠ የሚለውን የምዕራፍ 5፥20 ጥቅስ መነሻ ሀሳብን በማጣመም “ሀጢዐታችን የቱንም ያህል ቢከፋ ፀጋ ሀጢዐት በልጦ ስለተገኘ ብዙ ሀጢዐት ባደረግን ቁጥር የእግዚአብሔር ፀጋ አብልጦ ይበዛልናል” በማለት አማኞች ፀጋን ስለተገዳደሩ ጳውሎስ በክርስቶስ በማመን በፀጋ አማካኝነት ሁሉም ሀጢያታችን ይቅር ስለተባለ ፀጋ የፈለግነውን እንድናደርግና በስነምግባር ብልሹ ሆነን እንኖር ዘንድ ነፃነትን አይሰጠንም ልቅ ነፃነት የልቅ ግድየለሽነት ውጤት ነውና ይላል። ፀጋ አቅምና ጉልበት የሆነን ለመተላለፍና በእግዚአብሔር ምሕረት ላይ ለመረማመድ ሳይሆን ሐጢዐትን አሻፈረኝ በማለት ለጌታ ክብር የሆነ ሕይወት እንድንኖር ነው። ከጌታ ሞትና ከጌታ ትንሳኤ ጋር ስለተባበርን ሐጢዐትን ማገልገል እንዳንችል ሆነን ዳግመኛ ተፈጥረናል። ከፀጋውም በታች ስለሆንን ፀጋ ይገዛናል፤ ፀጋ ከገዛን ሐጢዐት ሊገዛን አለመቻሉ ብቻ ሳይሆን ከሕግም በላይ እንድንራመድ አድርጎል። ሞቱን በሚመስል ሞት አሮጌው ስጋ በመሰቀሉ የኃጢአት ሰውነት ሀይል እንዲያጣና የጌትነት ስልጣን በእኛ ላይ እንዳይኖረው አድርጓል። ስለዚህ ከሀጢአት ነፃ የወጣን የፅድቅ ባሮች ነን ፀንተን ልንኖር ዳግም በባርነት ቀንበር እንዳንያዝ ልንጠነቀቅ ይገባል።
Comments