ሐዋርያው ዮሐንስ ጌታችንን የእግዚአብሔር ቃል፣ የአለማት ፈጣሪ፣ፍቅር፣ የእግዚአብሔር ስጦታ፣ መሲሕ፣ ሙሽራ፣ ብርሐን፣ ከፍተኛ ገዢ፣ የእግዚአብሔር ምሳሌና አዳኝ በማለት ሲያስተዋውቀን ከቆየ በኋላ ምዕራፍ አስር ላይ "ክርስቶስን መልካም የበጎች እረኛ ነው" ብሎ ይለዋል። የእረኛ መፅሐፍ ቅዱሳዊ ፍቺ የተከበረ የእግዚአብሔር ሕዝብ ጠባቂ ማለት ሲሆን በብሉይ ኪዳን ከተነሱት ታላላቅ የእግዚአብሔር ሰዎችና መሪዎች መካከል አብርሐም፣ ኖኅ፣ ይስሐቅ፣ ሙሴና ንጉሥ ዳዊት እረኞች ወይንም ከበጎች ጋር የተያያዘ ታሪክ እንደነበራቸው መፅሐፍ ይነግረናል።በተለይም ስለ ንጉሥ ዳዊት በሕዝቅኤል መጽሐፍ ላይ "በእነርሱ ላይ አንድ እረኛ ባርያዬን ዳዊትን አቆማለሁ እርሱም ያሰማራቸዋል እረኛቸውም ይሆናል” ተብሎ በሕዝቡ ላይ መሪ ሆኖ እንደሚሾም የትንቢት ቃል የተነገረለት መሆኑ እረኛ ስለሚለው ቃል ጥልቅ ፍቺ ይሰጠናል።እስከዛሬም ድረስ በተለይ በመካከለኛው ምስራቅ እረኞች ከፊት ከፊት እየሔዱ በጎቻቸውን መምራት፣ ለበጎቻቸው ስም መስጠት፣ አዲስ የተወለዱ ጠቦቶችን አቅፎ ከመንጋው ጋር መጓዝና በጎች ወደ በረት ከገቡ በኋላ በበረቱ በር ላይ በመተኛት በጎቹ እንዳይወጡ አውሬም ከውጭ ወደ ውስጥ ገብቶ ጥቃት እንዳያደርስ መከላከል የተለመደ ነው። በመዝሙር 80:1ላይ ላይ እስራኤላውያን ትድግናን ከእግዚአብሔር በፈለጉበት ግዜ "ዮሴፍን እንደ በግ መንጋ የምትመራ የእስራኤል እረኛ ሆይ ስማን ብለው ዘምረው እንደነበርም ይታወቃል። ባለቅኔውና ዘማሪው ንጉሥ ዳዊትም እስራኤልና ሕዝቧን እግዚአብሔር በታደጋቸውና በረዳቸው ቁጥር ይዘምሩት ዘንድ በተቀኘው ቅኔው መዝሙር 23 ላይ"እረኛዬ" የሚለውን የማዕረግ ስም መነሻው አድርጎ በሁኔታዎች አስገዳጅነት ከቶም የማይቋረጠውን የአምላክ ተንከባክቦ፣ መግቦትና ጥበቃን የሚገልፀው "እግዚአብሔር እረኛዬ ነው የሚያሳጣኝ የለም። በለመለመ መስክ ያሳርፈኛል፤ በእረፍት ውሀም ዘንድ ይመራኛል። ነፍሴን መለሳት ስለ ስሙም በፅድቅ መንገድ መራኝ" ብሎ በማለት ነው። ሐዋርያው ዮሐንስም ይሕንን ዳዊት የተናገረለትን የእግዚአብሔር ልጅ የሆነውን የክርስቶስን መልካም እረኝነት ነው በዚሁ መልዕክቱ እየነገረን ያለው።
በኖኅ ዘመን ኖኅንና ቤተሰቡን ከሞትና ከጥፋት የታደገው በር (እግዚአብሔር ከበስተኋላው የዘጋው በር) የነበረው ጌታ ክርስቶስ አሁን ደግሞ ከቅጥረኛ ይልቅ አብዝቶ ስለ በጎቹ ግድ የሚለው የዘለዓለም ሕይወት የምናገኝበት ወደ መንግሥተ ሠማያትም የምንገባበት የሕይወት በር ሆኖ እንደመጣ ፀሐፊው ያሳስበናል። በዚህ እረኛ መሪነት ካልሆነ በስተቀር ማንም የእግዚአብሔርን መንግስትና ልጅነትን ማግኘት አይቻለውም። የእግዚአብሔር ቃል አስረግጦ እንደሚናገረው ድነት በሌላ በማንም አይገኝም፤ እንድንበት ዘንድ ለሰዎች የተሰጠ ከዚህ ስም በስተቀር ሌላ ስም ከሰማይ በታች የለም። በዚህ ወንጌል የተበሰረው ሌላው ታላቅ የተስፋና የቃል ኪዳን ቃል ክርስቶስ ራሱ ለእስራኤላውያን መዳን ብቻ የመጣ አለመሆኑን ያበሰረበት "ከዚህ በረት ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ እነርሱን ደግሞ ላመጣ ይገባኛል ድምፄን ይሰማሉ አንድም መንጋ ይሆናሉ" ብሎ በማለት እረኝነቱ በስሙ ላመኑ የሰው ልጆች ሁሉ እንደሚሆን በመጨረሻም አይሁድም አሕዛብም በክርስቶስ አንድ የእግዚአብሔር መንጋ እረኛቸውም እርሱ አንዱ ጌታ ክርስቶስ መሆኑን ማብሰሩ ነው።
コメント